#Ethiopia | በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ለ3 ሺሕ 611 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጋቸውን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጉዮ ዋሪዮ ጉዳዩ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ለታራሚዎቹ ህጉን መሰረት በማድረግ እና የክልሉ የይቅርታ ቦርድ በየደረጃው ማጣራት አድርጎ ለርዕሰ መስተዳድሩ በማቅረብ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን ገልጸዋል፡።
ይቅርታ ከተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች መካከል 3 ሺሕ 334 ወንዶች ሲሆኑ 247 ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።
ታዳጊ ታራሚዎች ሆነው አንድ አራተኛ የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ እና ልጅ ይዘው በማረሚያ ቤት የሚገኙ እንዲሁም ነፍሰጡር ሴቶች ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል መሆናቸውንም ዐቃቤ ህጉ ገልጸዋል።
ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ባህሪ ማሳየታቸውና ከቅጣቱ መማራቸው በሚመለከተው አካል የተረጋገጠ መሆኑንም አንስተዋል።
በተጨማሪም እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶችና የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ከ10 ዓመት በላይ በማረሚያ ቤት ያሳለፉ ይቅርታ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።
ይቅርታው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው፣ በተደጋጋሚ ወንጀል የተሳተፉ፣ ዘረፋ፣ በሙስና እና በአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች የተሳተፉትን እንደማይመለከት ማስረዳታቸውንም #ኢዜአ ዘግቧል።