የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግምጃ ቤት ሰነዶች (Tbills) የወለድ ምጣኔ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱንና ለመጀመሪያ ጊዜ ከፖሊሲ ምጣኔ በላይ መሆኑን አስታውቋል፣ ይህም አዎንታዊ ምጣኔን ያመለክታል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካቲት 6፤2017 ዓ.ም. ባሳተመው አጭር ሪፖርት መሠረት የአንድ ዓመት የግምጃ ቤት ሰነዶች የወለድ ምጣኔ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ57 በመቶ ጨምሯል።
በሐምሌ ወር 10 በመቶ የነበረው ምጣኔ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ 15.7 በመቶ ከፍ ብሏል፣ ይህም ጥር ላይ ከተመዘገበው የ15.5 በመቶ የዋጋ ግሽበት እና የ15 በመቶ የፖሊሲ ምጣኔ አንጻር ከፍተኛው መጠን ሆኖ እንዲቀመጥ ያደረገ ነው።
በቲ-ቢል ምጣኔዎች ላይ የቅርብ ጊዜ ጭማሪ የአለም አቀፋዊ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ ) የሚሰጠውን ምክር ተከትሎ የመጣ ሲሆን፣ ይህም ማዕከላዊ ባንክ ተጨማሪ ተጫራቾችን ለመሳብ እና ሀብት ለማሰባሰብ የሚረዳ መሆኑ ነው አይኤምኤፍ ሲገለጽ የቆየው፡፡
አሁን ላይ የተቀማጭ ወለድ ከግሽበት አንጻር በከፍተኛ መጠን ቅናሽ ያለው መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በተመሳሳይ የመግስት የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ ላይ ማእከላዊ ባንኩ የሚቀበለው የወለድ ምጣኔ ከ10 በመቶ አይበልጥም ነበር፡፡
በመሆኑም ከፍ ያለ ወለድ የሚጠይቁ ተጫራቾች በጨረታው አያሸንፉም ነበር፡፡ ሆኖም ባለፉት ጥቂት ወራት ባንኩ ከፍ ያሉ የወለድ መጠኖችን እየተቀበለ መምጣቱ ነው የሚነገረው።